በሀገራችን የሙዚቃ ታሪክ እጅግ መቀዛቀዝ፣ የሙዚቃ አልበምም ህትመት መፍዘዝ፣ ፊልም ሰሪዎችም “አረ ጉድ ነው የሰው ያለህ” ባሉበት በዚያ ወቅት እንደ አንድ የኪነጥበብ አባልና የሚዲያ ሰው የበኩላችንን አስተዋጽኦ ለማበርከትና አድማጭ ተመልካቹን ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ ለማነቃቃት በማሰብ ነበር በሸገር ኤፍ ኤም 102.1 የለዛ የአድማጮች ምርጫ ሽልማት ስነስርዓት የተጀመረው፤ ከዚህ ባለፈ ምንም እንኳ በሀገራችን ብዙ አስርት አመታት ያስቆጠረ ባህላዊም ሆነ ዘመናዊ የኪነጥበብ ልማድና ስራ ቢኖረንም ቅሉ እነኚህን የኪነ ጥበብ ሰዎችና ስራዎች ተከታትሎ በተገደበ የጊዜ ኡደት እውቅና የሚሰጥ “ቋሚ” ተቋም በመጥፋቱ ምክንያት: “ለምን እኛ የቻልነውን አናደርግም” የሚልም ነበር ሌለኛው የመነሻ ሃሳባችን፣ “የኪነጥበብ ሰዎች በአመት አንድ ጊዜ በህብረት ተገናኝተው የሆድ የሆዳቸውን እየተጨዋወቱ ቢያመሹ፣ ለአዲስ መጪዎቹ ልምድ ማግኛ፣ ለአንጋፋዎቹም ትውልድ ማፍሪያ፣ አይሆንም ወይ? የሚለው ጥያቄም አይዘነጋም፤
እነዚህን ዋነኛ ገፊ ምክንያቶች አስቀድሞ በ2003 ዓ.ም የአመቱ ምርጥ ነጠላ ዜማ፣ ምርጥ ተዋናይት፣ የአመቱ ምርጥ ተዋናይ፣ የአመቱ ምርጥ ፊልምና የአመቱ ምርጥ አልበም በሚሉ አምስት ዘርፎች የመጀመሪያው በሸገር ኤፍ.ኤም 102.1 የለዛ ሬዲዮ ፕሮግራም የአድማጮች ምርጫ ሽልማት ስነስርዓት በሚል ስያሜ የሀገራችን የኪነጥበብ ሰዎች በተገኙበት በታሪካዊው የብሔራዊ ቴያትር አዳራሽ በደማቁ ተካሄደ፤
ዘሪቱ ከበደ "አርተፊሲያል" በሚለው ነጠላ ሙዚቃዋ፣ ሰሃር አብዱልከሪም “ያንቺው ሌባ” በተሰኘ ፊልም ላይ ባሳየችው ትወና፣ ጋሽ አበበ ባልቻ በሄሮሺማ፣ ራሱ ሄሮሺማ ደግሞ በምርጥ በፊልምነቱ፣ ናትናኤል አያሌው (ናቲ ማን) “Man” ብሎ በሰየመው የመጀመሪያ አልበሙ በየ ውድድር ዘርፎቹ ቀዳሚ አሸናፊዎች ሆነው በለዛ የታሪክ መዝገብ ላይ ሰፈሩ፤
በየአመቱ ከጥቅምት ወር ጀምሮ እስከ ሃምሌ ድረስ የሚወጡ የኪነጥበብ ሰዎችንና ስራዎችን በአድማጮች ምርጫ አወዳድሮ እውቅና ለመስጠ በ2003ዓ.ም አንድ ያለው ለዛ፤ በ2004ዓ.ም መስከረም ወር ላይ ሁለትኛውን የጥበብ ድግስ በነዛው አምስት የውድድር ዘርፎች በተሳካ ሁኔታ በእንቢልታ የሲኒማ አዳራሽ ሲያካሂድ፤ ማህደር አሰፋ ምርጥ ተዋናይት በሼፉ ፣ ታሪኩ ብርሃኑ(ባባ) በፍቅር ኤቢሲዲ ምርጥ ተዋናይ፣ ራሱ የፍቅር ኤቢሲዲ የተሰኘው ፊልም ደግሞ የአመቱ ምርጥ ፊልም ሲሆን፣ ቴዋድሮስ ካሳሁን(ቴዲ አፍሮ) “ጥቁር ሰው” ብሎ የጠራው አልበሙ የአመቱ ምርጥ አልበም ተሰኝቶለታል፤ የጃሉድ “ድግስ” የአመቱ ምርጥ ነጠላ ዜማን ሽልማት እንዲወስድ አስችሎታል፤
በ2005 ዓም ለሶስተኛ ጊዜ ጣይቱ ሆቴል ግቢ ውስጥ በነበረው ተወዳጁ ጃዝ አምባ አዳራሽ የተካሄድው በሸገር ኤፍ.ኤም 102.1 የለዛ ሬዲዮ ፕሮግራም የአድማጮች ምርጫ ሽልማት ስነስርዓት ከቀደሙት ሁለቱ እጅግ በበዛ ድምቀት የተካሄደ ሲሆን በታዳሚም ብዛት የላቀ ነበር፤ በዝግጅቱም የኛ የተሰኘው ሙዚቃ በነጠላ ዜማ ዘርፍ፣ ማህደር አሰፋ በአይራቅ ፊልም ምርጥ ተዋናይት፣ ሳምሶን ታደሰ ቤቢ በአምራን ፊልም ምርጥ ተዋናይ፣ አይራቅ የአመቱ ምርጥ ፊልም፣ የሚካኤል በላይነህ ናፍቆትና ፍቅር የተሰኘው አልበም ደግሞ የአመቱ ምርጥ አልበም ተብለው ተሸልመዋል፤
በ2006ዓ.ም ሰሜን ሆቴል በሚገኘው የኢጣሊያዊያን የባህል ማዕከል አዳራሽ የተካሄደው አራተኘው በሸገር ኤፍ ኤም 102.1 የለዛ አመታዊ የአድማጮች ምርጫ ሽልማት ስነስርዓት ከቀደሙት ሶስት ዝግጅቶች በአቀራረብም በአይነትም ለየት ብሎ የተካሄደ ሲሆን ሶስት አዳዲስ የውድድር ዘርፎችን ማለትም የህይወት ዘመን፣ ምርጥ አዲስ ድምጻዊ እና የአመቱ ምርጥ የሙዚቃ ቪዲዮን በማካተት የውድድር ዘርፎቹን ወደ ስምንት በማሳደግም ጭምርም ነበር፤
ሩታ መንግስተዓብ በረቡኒ ምርጥ ተዋናይት፣ መሳይ ተፈራ በትመጫለሽ ብዬ ፊልም ምርጥ ተዋናይ፣ ታላቅ ወንድሙ ግርማ ተፈራ በመቼ ትመጫለሽ ሙዚቃው ምርጥ ነጠላ ዜማን፣ የስለሺህ ደምሴ (ጋሽ አበራ ሞላ) ያምራል ሀገሬ ምርጥ አልበም፣ የቅድስ ይልማ ረቡኒ የአመቱ ምርጥ ፊልም፣ ሚካኤል ለማ ደምሰው እና ጃኪ ጎሲ በፊያሜታ የሙዚቃ ቪዲዮው ሁለቱን አዳዲስ ዘርፎች ማለትም ምርጥ አዲስ ድምጻዊንና ምርጥ የሙዚቃ ቪዲዮን ሲያሸንፉ፣ የኢትዮዺያ ዘመናዊ ሙዚቃ ላይ የማይረሳ ታሪክ ካሳረፉት ከዋክብት መሃከል ዘመን ተጣማሪዎቹ ባለ ማንዶሊኑ “ነፍስ ኄር” ጋሽ አየለ ማሞና የትዝታው ንጉስ ጋሽ ማሃሙድ አህመድ በጣምራ በህይወት ዘመን ዘርፍ ተሸላሚ ሆነው አልፏል፤
“ምርጥ የፊልም ማጀቢያ ሙዚቃ” የሚለው አዲስ የሽልማት ዘርፍ የተካተተበት የሽልማት ዘርፎቹም ወደ ዘጠኝ ያደጉበት በይዘቱ ገዝፎ በአቀራረቡ ከመቼውም ጊዜ በላይ ደምቆ የታየው፣ በተንጣለለው የሂልተን ሆቴል ቦል ሩም የተካሄደው የ2007ቱ አምስተኛው በሸገር ኤፍ ኤም 102.1 የለዛ ሬዲዮ ፕሮግራም የአድማጮች ምርጫ ሽልማት ስነስርዓት ነበር፤
ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) “በሰባደረጃ” የተሰኘው ነጠላ ሙዚቃው ምርጥ ነጠላ ዜማን፣ አኒሜትድ የሆነውና በፊቸሪንግ ጃሉድ የተሳተፈበት የዮሴፍ ገብሬ(ጆሲ) “ሽክ ብለሽ” የተሰኘው የሙዚቃ ቪድዮ የዓመቱ ምርጥ የሙዚቃ ቪዲዮ፣ ድምጻዊ ዳን አድማሱ ምርጥ አዲስ ድምጻዊ፣ አዚዛ አህመድ በሰኔ ሰላሳ ምርጥ ተዋናይት፣ ግሩም ኤርሚያስ በላምባ ፊልም ምርጥ ተዋናይ፣ ሰኔ ሰላሳ የዓመቱ ምርጥ ፊልም፣ የአብነት አጎናፍር አስታራቂ ምርጥ አልበም፣ በአዲሱ ምርጥ የፊልም ማጀቢያ ሙዚቃ ዘርፍ ለኻረየት ፊልም ማጀቢያነት የተሰራው የጼደኒያ ገብረ ማርቆስ ሙዚቃ ተሸላሚ ሲሆን፣ ቄንጠኛው፣ የሃበሻው ጀምስ ብራውን “ነፍስ ኄር” አንጋፋው ጋሽ አለማየሁ እሸቴ በህይወት ዘመን ሽልማት ዘርፍ ተሸላሚ ሆኖ ተጠናቋል፤
ድምጻዊ ሳሚ ዳን በአራት የሽልማት ዘርፎች ታጭቶ አራቱንም ሽልማቶች የወሰደበት በዛው በሂልተን ሆቴል ቦል ሩም በ2008ዓ.ም የተካሄደው ስድስተኛው በሸገር ኤፍ.ኤም 102.1 የለዛ ሬዲዮ ፕሮግራም የአድማጮች ምርጫ ሽልማት ስነስርዓት ከወትሮው ልዩ ነበር፤ በዚህ ዝግጅት በምርጥ አዲስ ድምጻዊነት፣ በምርጥ የሙዚቃ ቪዲዮ፣ በምርጥ ነጠላ ዜማ እና እንዲሁም በታላቁ ሽልማት ዘርፍ በምርጥ የአመቱ አልበም የሳሚዳን “ከራስ ጋር ንግግር” አልበም እና
በውስጡ የተካተተው ባለ ቪዲዮው “ጠፋ የሚለየን” ነጠላ ዜማ በሽልማት ተንበሽብሸው አምሽተዋል፤ በተጨማሪም አዲስ አለም ጌታነህ እና ካሳሁን ፍሰሃ(ማንደላህ) ሁለቱም በሀእና ለ ፊልም ምርጥ ተዋናይትና ተዋናይ፣ የአብርሃም ገዛህኝ የነገን አልወልድም የአመቱ ምርጥ ፊልም ተብለው ሲሸለሙ ደርባባውና
ዘናጩና ባለ ውብ ድምጹ ጋሽ ተሾመ ምትኩ የህይወት ዘመን ዘርፍ ተሸላሚ ሆኖል፤
ሁለት ጥንዶች እጩ የሆኑበትና እውቁ ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን(ቴዲ አፍሮ) በሁለት ዘርፎች ታጭቶ ሁለቱንም ሽልማቶች የወሰደበት አሁንም በዛው በሂልተን ሆቴል ቦል ሩም የተካሄድው የ2009ኙ ሰባተኛው በሸገር ኤፍ.ኤም 102.1 የለዛ ሬዲዮ ፕሮግራም የአድማጮች ምርጫ ሽልማት ስነስርዓት ከቀደሙት ዝግጅቶች ሁሉ የብዙዎችን ትኩረት የሳበና የገዘፈ የሚዲያ ሽፋን ያገኘ ነበር፤
ይህም የፕሮግራሙን አዘጋጆች የጅማሬ ትልም የመታና በመላው የጥበብ ስራ ላይ ተጽእኖ መፍጠር የሚያስችል አቅም ያስገኘ አስደሳች ሁኔታ ነበር፤ በተወዳዳሪ እጦት ከአምስተኛው በሸገር ኤፍ.ኤም 102.1 የለዛ የአድማጮች ምርጫ ሽልማት ስነስርዓት አልፎ መጓዝ ያልቻለው “የአመቱ ምርጥ የፊልም ማጀቢያ ሙዚቃ” ዘርፍ ባይቀነስ ኖሮ በሰባተኛው ዝግጅት ላይ አዲስ ሆኖ የገባው ምርጥ ተከታታይ የቴለቪዥን ድራማ ዘርፍ የሽልማቱን ዓይነት ወደ አስር ያሳድገው ነበር፤
ዘመን የተሰኘው ተከታታይ የቴሌቪዥን ፊልም በአዲሱ ምርጥ ተከታታይ የቴለቪዥን ድራማ ዘርፍ፣ድምጻዊ ዳዊት አለማየሁ በምርጥ አዲስ ድምጻዊ ዘርፍ፣ ብስራት ሳሙኤል “ሄድ መለስ” በተሰኛው ቪድዮ ባካተተው ነጠላ ዜማው በምርጥ የሙዚቃ ቪዲዮ ዘርፍ፣ ድምጻዊት ዘሪቱ ከበደ በታዛ ፊልም ትወናዋ በምርጥ የአመቷ ተዋናይት ዘርፍ፣ አለምሰገድ ተስፋዬ በምርጥ የአመቱ ተዋናይ ዘርፍ፣ እውቁ ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) (አሁን ክቡር ዶክተር) “ኢትዮዺያ” ብሎ በጠራው አልበሙና ቀደም ብሎ ባወጣው የአልበሙ መጠሪ ነጠላ ዜማ በሁለቱ የውድ ድር ዘርፎች ማለትም በዓመቱ ምርጥ የሙዚቃ አልበምና በምርጥ ነጠላ ዜማ ዘርፍ፣ የቅድስት ይልማ ታዛ ፊልም በምርጥ የአመቱ ፊልምነት አሸንፈው የተዘጋጀላቸውን ሽልማት ሲወስዱ፣
የኢትዮዺያ ሙዚቃ ወርቃማ ዘመን ሁነኛ ማስታወሻና ህያው ምስክር የሆነው አንጋፋው የሙዚቃ ሰው ጋሽ ግርማ በየነ የህይወት ዘመን ዘርፍ ተሸላሚ ሆኖ ተጠናቃል፤
ውድ ሃገራችን በገጠማት የፖለቲካ ምስቅልቅል ምክንያትና ያም ሁኔታ መላው ህዝብ ላይ በፈጠረው ጭለማ ስሜት ምክንያት ኡደቱን ጠብቆ በአመቱ ጥቅምት ወር ላይ በ2010 ዓ.ም መካሄድ የነበረበት 8ንተኛው መርሃ ግብራችን መታሰቢያነቱን በፖለቲካው ምስቅልቅል ምክንያት ህይወታቸውን ላጡ የሀገራችን ዜጎች አድርጎ በተደበተ ስሜት አንድ ዓመት ዘግይቶ ጥቅምት 13 2011 ዓ.ም ነበር የተካሄደው፣
ወጣቱ ከያኒ ሮፍናን በሶስት ዘርፎች በምርጥ አዲስ ድምጻዊ፣ በምርጥ ነጠላ ዜማና በምርጥ አልበም የአድማጮችን ይሁንታ አግኝቶ በሽልማት የተንቆጠቆጠ ሲሆን፣ ናቲ ማን በምርጥ ቪዲዮ፣ተዋንያኑ አለማየሁ ታደሰና አዚዛ አህመድ፣ የየጾታቸው ምርጥ ተዋኒያን ተሰኝተው አምሽተዋል፤
ምን ልታዘዝ የተሰኘው ፊልም በምርጥ ተከታታይ የቴሌቪዥን ፊልም ዘርፍ፣ ድንግሉ የተሰኘው ፊልም ደግሞ በአመቱ ምርጥ ፊልምነት የለዛን ሽልማት ወስደው ከብረዋል በምሽቱ፤ የኢትዮዺያ ሙዚቃ የምንግዜም ባለ ውለታ ባለ ወርቅ ብዕሩ ይልማ ገብረአብን በሂወት ዘመን ዘርፍ ታዳሚ የነበረው የጥበብ ቤተሰብ ቆሞ አመስግኖታል፤
አንድም የሀገራችን የጥበብ ሰው የቀረ የማይመስልበት ያ ውብ ምሽት ለኛ ለአዘጋጆቹ ሀሴትን ቢፈጥርልንም ቅሉ ለቀጣይ ቆንጆ የሆነ የቤት ስራ ጥሎልን አልፎል፤
ከወትሮ እጅግ በተለየ ስሜትና መነቃቃት የካበተ ልምድና የበዙ በጎ አድራጊዎችን ይዘን በጠነከረ የእናድርገው ስሜት የጀመርነው ዘጠነኛው የለዛ የአድማጮች ምርጫ ሽልማት ስነስርአት ጥቂት ጊዜያት ሲቀሩን በሰማነው እጅግ አስደንጋጭ የህልፈተ ህይወት ዜና እጅጉኑ ተረብሸን ነበር ያካሄድነው፤ ይኸውም በችሎታና በጥበቡ የተደነቀው፣ በአመለ ሸጋነቱ የተወደደው፣ በስራው ጥራትና ትጋት ሁሌም የሚደነቀው፣ በአበርክቶው ዘለዓለም የሚታወሰው፣ የዜማና ግጥም ደራሲው ፣ አቀናባሪው፣ የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋቹ ፣ የመብት ተሟጋቹ ብቻ የኢትዮዺያ ሙዚቃ ሁለገብ ሰውና ታላቅ ባለውለታ ክቡሩ፣ አንድ ለእናቱ ኤልያስ መልካ ገረሱን ማጣታችን ነበር፤
ሶስት አዳዲስ የውድድር ዘርፎች ማለትም ተከታታይ የቴሌቪዥን ፊልም ምርጥ ተዋናይት እና ተዋናይ እንዲሁም የአመቱ ምርጥ ዘፈንን የጨመረው ለዛ በጠቅላላው በ 12 ዘርፎች ነበር 9ኛውን መረሃግብር በጥቅምት ወር 2012 ዓ.ም ላለፉት አምስት አመታት አክባሪ አጋራችን በሆነው የሂልተን ሆቴል ቦል ሩም ያካሄድው፤
ተዋናይት ሃና ዩሃንስና ተወዳጁ ጋሽ አበበ ባልቻ ሁለቱም ከዘመን ከተሰኘው ተከታታይ የቴሌቪዥን ፊልም በአዳዲሶቹ የቴሌቪዥን ተከታታይ ፊልም ምርጥ ተዋናይትና ተዋናይ ዘርፍ ሲያሸንፉ፣ ደርሶ መልስ የተሰኘው ተከታታይ የቴሌቪዥን ፊልም በምርጥ ተከታታይ የቴሌቪዥን ፊልም ዘርፍ አሸናፊ ሆኗል፤ በሃይሉ ታደሰ (ዚጊዛጋ) በአዲሱ የአመቱ ምርጥ ዘፈን ዘርፍ ተሸላሚ ሆኗል፤
ቁራኛዬ የተሰኘው ፊልም የአመቱ ምርጥ ፊልም ከመባሉ በተጨማሪ መሪ ተዋናዮቹን የምስራች ግርማ እና ዘሪሁን ሙላትን በሁለቱም ዘርፍ ማለትም በአመቷ ምርጥ ተዋናይትና እና የአመቱ ምርጥ ተዋናይ ዘርፍ አሸናፊ ሆነውለታል፣ ታዋቂው ድምጻዊ ጎሳዬ ተስፋዬ ከእሀድ እስከ እሁድ ለተሰኘው ዜማው በሰራው ቪዲዮ የአመቱን ምርጥ የሙዚቃ ቪዲዮ አሸናፊ ሲሆን፣ ድምጻዊ ጃንቦ ጆቴ ተወዳጅነትን ባተረፈለት በልባ በተሰኘው ዜማው የአመቱ ምርጥ ነጠላ ዜማን ክብር ወስዷል፤
በብርሃናማው የኢትዮዺያ የሙዚቃ ዘመን ደማቅ ታሪክ ያለው የሮሃ ባንድ መስራችና የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋች የነበረው፣ ከዛም በኋላ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ ከተለያዩ ባንዶች ጋር በመስራትም ሆነ በመመስረት ተወዳጅነትና ተደናቂነት ያተረፈው፣ ብዙዎች “እሱን አይቼነው ቤዝ ጊታር ያነሳሁት” የሚሉለት፣ ልዩ አጨዋወትና መንገድ ይዞ ለሀገራችን ሙዚቃ የማይዘነጋ ውለታ የዋለው ዘመናዊው ሰው የእውነት አዋቂ ቤዚስትና ሙዚቀኛ ጆቫኒ ሪኮ በህይወት ዘመን ዘርፍ በዕለቱ የከበረ ሲሆን ድምጸ ምቹዋ ወጣቷ ድምጻዊት ቸሊና የሺወንድም በሁለት ዘርፍ ማለትም በአዲስ ድምጻዊና በታላቁ የሽልማት ዘርፍ በአመቱ ምርጥ አልበም ዘርፍ አሸናፊ ሆና መርሃ ግብራችን ተፈጽሟል፤
በለዛ የዘጠኝ ዓመታት ታሪክ ውስጥ ድምጻዊ ሳሚ ዳን አራት ጊዜ በመታጨትና በአንድ ጊዜ አራት ሽልማቶችን በመውሰድ የቀዳሚነቱን ስፍራ ሲቀዳጅ፣ ሌላኛው ወጣት ሙዚቀኛና ዜመኛ ሮፍናን በሶስት ዘርፎች በማሸነፍ ይከተላል፣ እውቁ ድምጻዊ፣ የዜማና የግጥም ደረሲ አሁን ደግሞ ክቡር ዶክተር ቴዎድሮስ ካሳሁን(ቴዲ አፍሮ)፣ ተወዳጇ አዲስ ድምጻዊት ቸሊና የሺወንድም እና ተዋናይት ማህደር አሰፋ ሁለት ሁለት ጊዜ በማሸነፍ ሳሚ ዳንን እና ሮፍናንን ይከተላሉ፤
በቅን ሃሳብ ተነስቶ፣ በመልካም አድራጊ በጎ ሰዎች ጎልብቶ፣ ዘወትር ፊታቸው በማይጠቁር አጋሮቻችችን ጸንቶ፣ በጥበብ ሰዎች ደምቆ፣ ይልቁንም በእናንተ አድማጭ ተመልካቾቻችን ሰናይ ምክርና አራሚ ተግሳጽ በርትቶ፣ እነሆ 2003ዓ.ም ላይ አንድ ያለው ለዛ ይኸው ዘንድሮ 10 ሊል ነው፤
ዓለምን ከሰርክ ምልልሱ ለሁለት ዓመታት የሚካል ጊዜ ባዘናጋው፣ ልማዳዊ ሰላምታችንን ሳይቀር በቀየረብን፣ ጦሱ አሁንም አለቅም አለሁ እያለ በሚያስፈራራን ኮቪድ-19 የተሰኘ ሳይንሳዊ ስያሜ በያዘው ወረርሺኝ ምክንያትና አገራችንም ሠላሟ በመደፍረሱ የሚል ለዛ የተለመደውን የጊዜ ኡደት ጠብቆ አመታዊ ባአሉን ሳያከብር ሁለት አመታትን ለመጠበቅ ተገዶ ነበር፤
እነሆ አሁን ጊዜው ደርሷል፤
እንኳን ደስ ያለን እንኳን ደስ ያላችሁ፤
ሁለት አመታት በመዘግየቱ ምክንያት አስረኛውንና አስራ አንደኛውን በጋራ ሁለቱን አጣምረን “10ኛውና 11ኛው በሸገር ኤፍ ኤም 102.1 የለዛ አድማጮች ምርጫ ሽልማት” ስነስርአት ብለን በሰጠነው ስያሜ መሰረት በ- -- -- ወር 2014 ዓ.ም ላይ በተለመደው የተንጣለው የሂልተን ሆቴል ቦል ሩም ልናሰናዳው በተዘጋጀንበት የለዛ አድማጮች ሽልማት ፕሮግራም ከመቼው ጊዜ በላይ ባካበትነው ልምድ ታግዘን በተለመዱት አስራ ሁለት የውድድር ዘርፎች ማለትም
በምርጥ ተከታታይ የቴሌቪዥን ፊልም
በተከታታይ የቴሌቪዥን ፊልም ምርጥ ተዋናይት
በተከታታይ የቴሌቪዥን ፊልም ምርጥ ተዋናይ
በአመቱ ምርጥ ፊልም
በአመቱ ምርጥ የፊልም ተዋናይት
በአመቱ ምርጥ የፊልም ተዋናይ
በአመቱ ምርጥ የሙዚቃ ቪዲዮ
በአመቱ ምርጥ ዘፈን
በአመቱ ምርጥ ነጠላ ዜማ
በአመቱ ምርጥ አዲስ ድምጻዊ
በህይወት ዘመን ተሸላሚ እና
በአመቱ ምርጥ የሙዚቃ አልበም ዘርፎች ከሃምሌ 1 2011ዓ.ም እስከ ሰኔ 30 2013 ዓ.ም ለሁለት ዓመታት የወጡትን የጥበብ ስራዎችና የጥበብ ሰዎች የምናወዳድር ይሆናል፣ ከወዲሁ ቢያሸንፍ፣ በመድረኩ ቢከብር ደስ ይለናል ለምትሉት የጥበብ ሰውና ስራዎች ድምጽ እንድትሰጡ፣ ይሁን ስንል አክብረን እንጋብዛለን፤
በሸገር ኤፍ ኤም 102.1 የለዛ ሬዲዮ ፕሮግራም የአድማጮች ምርጫ ሽልማት አዘጋጆች 2014 ዓ.ም
አዲስ አበባ!!